Skip to main content
ብዝሃነትን በአግባቡ ለማስተናገድ ህብረብሔራዊ የፌዴራል ስርዓትን በመከተል አማራጭ የሌለዉ ጉዳይ ነው

ሕዳር 28/2016 ዓ.ም የሲዳማ ክልል ምክር ቤት ብዝሃነትን በአግባቡ ለማስተናገድ ህብረብሔራዊ የፌዴራል ስርዓትን በመከተል አማራጭ የሌለዉ ጉዳይ መሆኑን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር ገለፁ።

18ኛዉን የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓልን መነሻ በማድረግ በጅግጅጋ ከተማ ኮንሶሲየሽናል ዴሞክራሲ፣ ጽንሰ ሀሳባዊ ዳራውና ኢትዮጵያዊ እሳቤዉ ላይ ሲምፖዚየም እየተካሄደ ነዉ።

የመደመር ቀን ተብሎ በተሰየመዉ የዛሬው ዕለት በሲምፖዚየም ሲከበር መልዕክት ያስተላለፉት የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር፣ የውጭና የውስጥ ኃይሎች በልዩነታችን ላይ በመመስረት ለግጭት እየጋበዙ ቢቆዩም ችግሮችን በዉይይት በመፍታት ለሀገራዊ ሰላም ሁሉም የድርሻዉን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

ኢትዮጵያ የብዝሃ ማንነት ባለቤት መሆኗን የጠቀሱት አፈ ጉባኤዉ የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን መከበር ህብረ ብሔራዊ ቀለማችንን ለመላዉ ዓለም የምናሳይበት የነፃነት ቀንዲል እንደሆነ ገልፀዋል።

በሲምፖዚየሙ የፌዴሬሸን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር፣ የባህልና ስፖርት ሚኒስትሩ አቶ ቀጀላ መርዳሳን ጨምሮ የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ ሙሀመድ፣ የክልል አፈ ጉባኤዎችና ርዕሰ መስተዳድሮች እንዲሁም የሁለቱ ከተማ አስተዳደር ከንቲባዎች በሲምፖዚየሙ እየተሳተፉ ይገኛሉ።

18ኛዉ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል “ብዝሀነትና እኩልነት ለሀገራዊ አንድነት” በሚል መሪ ቃል በነገዉ ዕለት በጅግጅጋ ከተማ በድምቀት ይከበራል።